የዜና ክምችት የዜና ክምችት

Back

የባቡር ትራንስፖርት ጭነቶችን በፍጥነት እና በብዛት እያጓጓዘ ነው፡፡

የባቡር ትራንስፖርት ጭነቶችን በፍጥነት እና በብዛት እያጓጓዘ ነው፡፡
********************
የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ኢትዮጵያን ከጅቡቲ ወደብ ጋር በማገናኘት የገቢና ወጪ ጭነቶችን በብዛት እና በፍጥነት በማጓጓዝ ቀድሞ የነበረውን ከፍተኛ የሎጅስቲክስ ወጪና ጊዜ በመቀነስ የኮሪደሩን የሎጅስቲክስ ሁኔታ ቀልጣፋ እንዲሆን እያደረገ ነው፡፡
የባቡር ትራንስፖርት በበጀት ዓመቱ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ 15 በመቶ እና የመልቲሞዳል ኮንቴይነሮችን ደግሞ 45 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እያጓጓዘ ሲሆን፣ በየቀኑ አንድ የማዳበሪያ እና ሁለት የኮንቴይነር አጓጓዥ ባቡሮች ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ በአንድ ጊዜም 2ሺህ 590 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ እና 110 ባለ ሃያ ጫማ (TEU) ኮንቴይነሮችን ያጓጉዛል፡፡
በተለይ አፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝን ስንመለከት ባለፈው ዓመት በአጠቃላይ 30 የባቡር ምልልስ ተደርጎ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት እ.ኤ.አ በጃዋሪ፣ ፌብርዋሪና ማርች 2021 በሶስት ወራት ብቻ 50 ምልልስ አድርጓል፡፡
ጭነቶችን በባቡር ማጓጓዝ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሉት ሲሆን በዋናነት በተሽከርካሪ እጥረት ጭነቶች ጅቡቲ የሚቆዩበትን ሁኔታ እየቀረፈ መሆኑ፣ የመርከቦች የወደብ ላይ ቆይታን በመቀነስ ተጨማሪ ወጪ እንዳይወጣ ማድረጉ፣ እንዲሁም ብትን ጭነቶችን እና ኮንቴይነሮችን በጊዜ በማንሳት ኢባትሎአድ ለዲመሬጅ /ተጨማሪ የወደብ ላይ ቆይታ) የሚያወጣውን ወጪ አስቀርቷል፡፡ በተጨማሪም ጭነቶች ከጅቡቲ በፍጥነት በሰዓታት ውስጥ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እያስቻለ ይገኛል፡፡
የባቡር ትራንስፖርት ከደህንነት አንፃርም ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር በተለይ ከጋላፊ እስከ አዳማ ድረስ ባለው የጉዞ ሂደት ጭነቶች ለተለያዩ ህገ-ወጥ ተግባራት ተጋላጭ በመሆናቸው ጭነቶችን በባቡር ማጓጓዝ ደህነንታቸው እንደተጠበቅ ለህገ-ወጥ ተግባራት ሳይጋለጡ መዳረሻቸው ድረስ የሚደርሱ በመሆኑ አገልግሎቱን ተመራጭ ያደርገዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ባቡር ከጅቡቲ ጭኖ ለመውጣት ከ2-3 ቀናት ይፈጅበት የነበረ ሲሆን ኢባትሎአድ ከኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጋር በከፍተኛ ቅንጅትና መናበብ በመስራቱ በዚህ ዓመት በአማካኝ ከ18-20 ሰዓት ብቻ ይወስዳል፣ ይህም ባቡሩ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ አስችሎታል፡፡
በአጠቃላይ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ከጊዜ፣ ከወጪ እና ከደህንነት አንፃር የተሻለ አገልግሎት በመስጠት ተመራጭ ነው::
ኢባትሎአድ