የዜና ክምችት የዜና ክምችት

Back

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ የሥራ ላይ ጉብኝት አደረጉ

 የትራንስፖርት ሚኒስትሩ የሥራ ላይ ጉብኝት አደረጉየትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ከ17/5/06-19/5/06 ዓ.ም ድረስ ለ3 ቀናት በትግራይና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች በመንግስትና በግል ተቋራጭ ድርጅቶች በግንባታ ላይ ያሉና ተገንብተው አገልግሎት እየሠጡ ያሉ መንገዶችን ጎብኝተዋል፡፡

ከተጎበኙት መንገዶች መካከል የዲማ ፍየል ውሃ 84 ኪሎ ሜትር በ938 ሚሊዮን ብር የአዘዞ ጎርጎራ 55 ኪሎ ሜትር መንገድ በ920 ሚሊዮን ብር ገመሹ በየነ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተሠኘ የግል ድርጅት በመገንባት ላይ ናቸው፡፡

ሌላው የአማራንና የትግራይን ክልል የሚያገናኘው የዛሪማ-ማይፀብሪ እና ማይፀብሪ ሽሬ መንገድ በኢትዮጵያ መንገድ ክንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እንደ አውሮፖውያኖቹ የዘመን ቀመር ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመገንባት ላይ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው፡፡

የዘሪማ-ማይፀብሪ መንገድ 70.7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው በሊማሊሞ በኩል የሚገኘውና አስቸጋሪ የሚባል የመሬት አቀማመጥ ያለው በኢትዮጵውያን ወጣት መሀንዲሶች ዲዛይን ተደርጎ እየተገነባ ነው፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ከ923 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡

የማይፀበሪ ሽሬ መንገድ 68.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው ከ 747 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በግንባታ ላይ የሚገኙትን ኘሮጀክቶች በጎበኙበት ወቅት በሊማሊሞ ግርጌ በሚገኘውና አስቸጋሪ ተፈጥሮአዊ የመሬት አቀማመጥ ባለው አካባቢ በሀገራችን ወጣት መሀንዲሶች ዲዛይን ተደርጎ መሰራቱ የሀገሪችን ኮንትራክተሮች በዘርፉ የደረሱበትን ደረጃ የሚያመለክት ሲሆን ሚኒስቴር መ/ቤቱ በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቁ የክትትልና ድጋፍ ሥራው አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብይ ገብረ ሚካኤል ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ ውሰጥ ካሉት አስቸጋሪ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ካላቸው ቦታዎች አንዱ መሆኑን ገልፀው ኮርፖሬሽኑ ከአሁን በፊት 6 ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለአገልገሎት ያበቃ ሲሆን በተያዘው ዓመት መጨረሻ ማይፀብሪ ሽሬና ማይፀብሪ ዛሪማ መንገዶችን ለአገልግሎት ያውላል፡፡ በቀጣይም ከሀገር ውጪ የምስራቅ አፍሪካ ገበያን እያጠኑ ሲሆን ከመንገድ በተጨማሪ በካናልና በታላላቅ ግድቦች ላይ ለመስራት አዳዲስ ቴክኖሎጂ በማስገባት ከተለያዩ ሀገራት ጋር እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡