የዕውነታ መግለጫዎች የዕውነታ መግለጫዎች

ትራንስፖርት ለኢኮኖሚያችንም ሆነ ለማህበራዊ ግንኙነታችን ወሳኝነት ያለው ዘርፍ ነው፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች ለአንድ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመፍጠርና ተጠናክሮ ለመዝለቅ፤ ህዝብን ከህዝብ በማገናኘት ለዲሞክራሲያዊ ሰርአት ግንባታ ወሳኝ የሆነ ዘርፍ ነው፡፡

የዚህ ዘርፍ መኖሩ ገጠሩን ከከተማ፣ ግብርናን ከኢንዱስትሪ ጋር ለማገናኘትና የኢኮኖሚ ትስስርን በማጠናከር አንድ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ የመፍጠሩን ጉዞ ለማሳካትና በአለም አቀፍ ገበያ ሊኖረን የሚገባውን ሚና ለመጫወት  ትልቅ እገዛ አለው፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በኢትዮዽያ በቀዳሚነት ከተቋቋሙ የሚኒስቴር መ/ቤቶች አንዱ የነበረ ቢሆንም በመጀመሪያ የተቋቋመው በትራንስፖርትና በመገናኛ ሚኒስቴር ነበር፡፡ አመሰራረቱ በ1886 ዓ.ም ንጉስ አፄ ሚኒሊክ አገሪቱን ከውጭው አለም ጋር የነበራትን ግንኙነት ለማጠናከር ብሎም ዘመናዊ የትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ወደ አገራቸው ለማስገባት በነበራቸው ጉጉት የባቡር ትራንስፖርት መስመር እንዲዘረጋ ጥርጊያ መንገዶች እንዲሰሩ ለማድረግ ከወሰዱት እርምጃ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡

በዚህ መልክ ተወጥኖ እያደገ በመሄዱ ላይ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት በ1928ቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ተደናቀፈ ተቋሙ በጦርነት ስለወደመ እንቅስቃሴው ከ1933-1942 ዓ.ም ባሉት ጊዚያት ተዳፍኖ ቆየ፡፡

ይሁንና በ1937 ዓ.ም የሲቪል አቪዬሽን አስተዳደር መቋቋም በ1938 ዓ.ም የኢትዮዽያ አየር መንገድ መመስረት፤ በ1943 ዓ.ም የኢትዮዽያ አውራ ጎዳና ባለስልጣን፤ በ1958 የባህር ማመላለሻ ድርጅት እንዲቋቋም መደረጉ የሴክተሩን ትንሳኤ ያበሰሩ ክንውኖች ነበሩ፡፡

ይህ የትራንስፖርት ተቋም ከመገናኛ ተቋም ጋር በራሳቸው አደረጃጀት እየተመሩ ቆይተው በ1966ቱ የመንግስትና የስርአት ለውጥ ሳቢያ ማእከላዊ አሰራርን ተከትለው እንዲዋቀሩ ተደረገ፡፡ የትራንስፖርትና መገናኛ አውታሮች ከቀድሞ በተለየና አገሪቱ ለምትከተለው የፌደራል ስርአትና በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አንፃር ባልተማከለ ሁኔታ እንደገና ተዋቅሮ የነበረው ከ1983 እስከ 1994 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ከዚያም ወዲህ ከ1994 እስከ 1998 ባሉት ጊዜያት በመሰረተ ልማት ሚኒስቴር ተተክቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በጥቅምት 1998 ዓ.ም የትራንስፖርት ሚኒስቴር በትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስቴር ስም በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን አደረጃጀቱንም መሰረት አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረ ተቋም ነው፡፡

በጥቅምት 17/2003 ዓ.ም የአስፈፃሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣ አዋጅ ቁጥር 691/2003 ትራንስፖርት ከመገናኛና ራሱን ችሎ የወጣ ሲሆን ተቋሙ በራዕይ እና በተልዕኮ ከቀድሞዎች አላማዎች የተለየ እዲሆን ተደርጓል፡፡

የትራንስፖርት ዘርፍ የትራንስፖርት ዘርፍ