የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች የCOVID-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ከመግታት አንፃር የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የመስክ ጉብኝት አደረጉ፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከዘርፉ ተጋላጭነት አንፃር በፌዴራልና በክልል በሁሉም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ የCOVID-19 ወረርሽኝ ለመከላከል እየተሰሩ ባሉት ስራዎች ዙሪያ የክትትልና ድጋፍ ስራን ያለማቋረጥ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም በምልከታዉ በትራንስፖርት ዘርፍ የአፈጻጸም መመሪያ መሰረት እየተጫነ ስለመሆኑ፣ ለተሳፋሪዎች የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራን፣ ርቀትን የማስጠበቅ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ በተደረግ የመስክ ምልከታ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በሁሉም አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ላይ የCOVID-19 ስርጭት ለመግታት የቁጥጥር ስራ የሚያከናውኑ ሰራተኞች በመመደብ እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት የቁጥጥር ስራውን በጋራ በመሰራት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሆኖም ግን በከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎችና ተጓዦች በCOVID-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተሳፋሪዎችን ቁጥር በግማሽ በመቀነሱ ምክንየት እንዲሁም የሚያስከፍሉት ታሪፍ ከፍ በማለቱ የተነሳ እና አዲስ አበባ ቀላል ባቡር የታሪፍ ለውጥ ባለመኖሩ በሌሎች ትራንስፖርት አገልገሎት ሲጠቀሙ የነበሩ ተጓዦች ወደ አዲስ አበባ ቀላል ባቡር በመምጣታቸው የተነሳ በጣቢያዎች መጨናነቅ መፈጠሩ ተስተውሏል፡፡
በመሆኑም የባቡር ተጠቃሚ በሚበዛባቸው ጣቢያዎች ላይ በተሳፋሪዎች መካከል ያለውን ርቀት ለማስጠበቅ በየፌርማታዎች የሚሰለፉ ሲሆን ወደ ባቡር በሚገቡበት ወቅት ሰልፍን እና እርቀትን በመጠበቅ እንዲገቡ እየተሞከረ ቢሆንም በየቀኑ የሚመጡ ሰዎች አዳዲስ ከመሆኑ አንፃር እና አካላዊ ርቀት የማስጠበቅ ስራ ላይ አሁንም ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ለማየት ተችሏል፡፡
በመሆኑም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ተጠቃሚዎች በሙሉ በሀገራችን እየጨመረ የመጣውን የወረርሽኝ ስርጭት ለመግታት የጤና ባለሙያዎችን የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ በማድረግ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል/ማስክ መጠቀም ፣ርቀትን መጠበቅን እንዲሁም ወደ ባቡር ጣቢያው ከመግባትዎ በፊት ድርጅቱ በሚያቀርበው ሳኒታይዘር/አልኮል እጅዎን በማፅዳት ራስዎን እና ማህበረሰቡን ከወረርሽኝ እንድከላከሉ በማለት መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

የዜና ክምችት የዜና ክምችት