‹‹የታዳሽ ሀይል ትራንስፓርት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ የምክክር መድረክ ተካሄደ

የትራንስፖርት ሚኒስቴር የታዳሽ ሀይል ትራንስፓርት በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡
የትራንስፖርት ሚንስትር ክብርት ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በምክክር መድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ከብክለት የፀዳ እና ለአካባቢ ተስማሚ እንዲሆን ለማድረግ፣ የግል ዘርፉን ማሳተፍ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑን ጠቅሰው የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪውን በማዘመን በኤሌክትሪክ እንዲሁም በነዳጅና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሸከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡና ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ የባለድርሻ አካላቱ ሚና የላቀ መሆኑን ግልጸዋል፡፡
አቶ ምትኩ አስማረ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ‹‹የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት በኢትዮጲያ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ፁኁፍ ሲያቀርቡ እንደገለጹት የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ጥቅም ላይ ማዋል ዋና አላማ ከብክለት የጸዳ፤ ቀጣይነት ያለው ተደራሽ የሆነ ትራንስፖርት ማቅረብን አለማ እንዳደረገ በገለጻቸው አስቀምጠዋል፡፡
የማራቶን ሞተርስ ኢንጂነሪንግ መስራች ባለቤትና ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መልካሙ አሰፋ እና የቶም ኢ-ባይክ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ቶማስ ሃይሉ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ ያቀረቡ ሲሆን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ምንም ዓይነት የበካይ ጋዝ ወይም የካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀትና የድምጽ ብክለት የማያስከትል መሆኑን ገልጸው ከተሻሻለው የኤክሳይስ ታክስ ጋር በተያያዘ መንግስት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ጥቅም ላይ እንዲውል እያደረገ ያለውን የማበረታት ስራ አድንቀዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በቀጣይ የተሻለ የትራንስፖርት አማራጮችን ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ከመንግስት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የዜና ክምችት የዜና ክምችት