መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ተጠቃሚ ለማድረግ የአሰራር ማንዋል ተዘጋጀ

ሀገራችን ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታትን ድርጅትን የአካል ጉዳተኞችን መብት ኮንቬክሽን ከፈረሙ ሀገራት መካከል ትገኛለች፡፡ ኮንቬክሽኑም አካል ጉዳተኞች ያለአንዳች አድሎ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተጠቃሚዎች ይሆኑ ዘንድ ዋስትና ይሰጣቸዋል፡፡ በሀገራችንም የህግ ማእቀፎችን በማሻሻል መስማት የተሳናቸው ዜጎች ባላቸው እውቀት እና ችሎታ በማንኛውም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ መሰረት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አዋጅ 1074/2010 መሰረት በማድረግ መስማት የተሳናቸው ሰዎች አሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ገብተው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና በመውሰድ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ማግኘት እንዲችሉ የአሰራር ማንዋል ተዘጋጅቷል፡፡
በአሁን ሰአት በመሰራት ላይ ያሉ ሰፋፊ የመንገድ አውታሮች ግንባታ፣ የአካል ጉዳተኝነትን ሊያስተካክሉ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤት ያካተቱ ተሽከርካሪዎች ለትራንስፖርት አገልግሎት እየዋሉ መሆኑ እና በምልክት ቋንቋ የአሽከርካሪዎችን ስልጠና መስጠት የሚቻል በመሆኑ እንደዚሁም የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥሩ ስርዓቱ መስማት ለተሳናቸው አመቺ በመሆኑ መስማት የተሳናቸውን ሰዎች የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ተጠቃሚ ማድረጉ በተሸከርካሪዎች ከቦታ ወደ ቦታ በመንቀሳቀስ የእለት ተእለት ስራዎቻቸውን ማከናወን እንዲችሉ ያደርጋል፡፡
ዋነኛው አላማውም መስማት የተሳናቸው ዜጎች የማሽከርከር መብታቸው ተረጋግጦ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ቀጣይና ዘላቂ እንዲሆን የራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ማድረግ እና ማሽከርከር አይችሉም በሚል የተሳሳተ አመለካከትና እና ግንዛቤ የሚፈጥረውን የስራ አጥነት ችግር በመቅረፍ ወደ አምራች ዜጋ መቀየር ነው፡፡
በመሆኑም መስማት የተሳናቸው ሰዎች አሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለማግኘት በአዋጅ 1074/2010 መሰረት ለየምድቦቹ የተቀመጠውን ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃና የማሽከርከር እድሜ ገደብ በማሟላት ማግኘት ይችላሉ፡፡

የዜና ክምችት የዜና ክምችት