ተሳፋሪዎች ወደ መናኽሪያ ሲመጡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ጭምብል) እንዲያደርጉ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ አሳሰበ፡፡

የተሳፋሪዎችን በቫይረሱ የመያዝ ተጋላጭነት ለመቀነስ ሕጉን ለማስፈጸም መገደዱን ቢሮው አስታውቋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 16/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ውቤ አጥናፉ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት ቢሮው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን የመከላከል ሥራ እያከናወነ ነው፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተካተቱት መካከል አሽከርካሪዎች ከተሽከርካሪው የመጫን አቅም በግማሽ እንዲያሳፈሩ፣ ሾፌሮች፣ ረዳቶች እና በየደረጃው ያሉ ሠራተኞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ጭምብል) እንዲለብሱ ያስገድዳል፡፡ ተሽከርካሪዎች በጸረ ተህዋሲያን እንዲጸዱ መደረግም አለባቸው፡፡ በመናኽሪያዎች እና በተሽከርካሪዎች ላይ የእጅ መታጠቢያ ውኃ፣ ሳሙና እና ማጽጃ ሳኒታይዘር እንዲዘጋጅ እየተደረገ መሆኑንም ነው ያመለከቱት፡፡
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ እነዚህን ሕጎች ለመተግበር ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ወደዕለት መጨመሩ ተጨማሪ ርምጃዎችን ለመውሰድ ግድ አድርጎታል፡፡
የተገልጋዮችን በቫይረሱ የመያዝ ተጋላጭነት ለመቀነስ ተሳፋሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ የተላለፈውን ሕግ ማስፈጸም ግድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እናም ወደ መናኸሪያ የሚመጡ ተገልጋዮች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መልበስ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። ተገልጋዮች ሕጉ ለራሳቸው ደኅንነት መሆኑን በመረዳት ለአፈጻጸሙ ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባም አቶ ውቤ አስታውቀዋል፡፡
ቢሮው ከቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ጋር በመተባበር ተሳፋሪዎች መናኽሪያዎች አካባቢ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ተሳፋሪዎች ደረጃውን የጠበቀ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ማግኘት ባይችሉ እንኳን ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመታደግ ባላቸው የልብስ ዓይነት አፍና አፍንጫቸውን መሸፈን እንደሚጠበቅባቸው ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
ሕጉን ከማስፈጸም ባሻገር ስለወረርሽኙ አስከፊነት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እየተሠራ መሆኑንም ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ

የዜና ክምችት የዜና ክምችት