የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት የስምሪት ሰዓት ማሻሻያ አደረገ

የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት የስምሪት ሰዓት ማሻሻያ አደረገ
የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የትራንስፖርት የስምሪት ሰዓት ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው መንግስት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ለአዲስ አበባ እና ለፌደራል ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ተግባራዊ ባደረገው የስራ መግቢያና መውጫ ሰአት መሰረት የትራንስፖርት ስምሪት ማሻሻያ አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት ጠዋት 1፡30 ወደ ስራ ለሚገቡ የፌደራል የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች የአውቶብስ መነሻ ሰዓት ቀደም ሲል በነበረው መርሃ-ግብር መሰረት እንደሚቀጥል የድርጅቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን አምባቸው ተናግረዋል።
ከረፋዱ 3፡30 ወደ ስራ ለሚገቡ የአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ደግሞ የጠዋት መነሻ ሰዓት ከጠዋቱ 2፡00 መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የፌደራል ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ከሥራ የመውጫ ሰዓት በመቀየሩ ወደ መኖሪያቸው ለማድረስ ከቀኑ 9፡30 ጀምሮ አውቶብሶቹ ቀደም ሲል በሚቆሙበት ቦታ ይጠብቃሉ።
ለአዲስ አበባ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞችም ማታ ወደ መኖሪያቸው ለማድረስ አውቶብሶቹ ከ11፡30 ጀምሮ ለትራንስፖርት ዝግጁ ሆነው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡
ድርጅቱ በአዲስ አበባ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍም ከ240 በላይ አውቶብሶችን ለታክሲ አገልግሎት ማሰማራቱንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ከነዚህ አውቶብሶች መካከለ ሃምሳዎቹ ያለክፍያ በነፃ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ድርጅቱ መንግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲልም በርካታ ሰራተኞች በቤታቸው እንዲቀመጡ የሰጠውን መመሪያ በመጣስ አንዳንድ ሠራተኞች ለግል ጉዳያቸው ሲንቀሳቀሱ አውቶብሶቹን እየተጠቀሙ መሆኑን ደርሸበታለሁ ብሏል።
በመሆኑም ለአንገብጋቢ የሥራ ጉዳይ ወደ ሥራ በሚገቡ ሠራተኞች ላይ ጫና እያሳደረ በመምጣቱ ከየመስሪያ ቤቶቻቸው ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡
በየትኛውም ስፍራ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚፈልጉ የጤና ባለሙያዎች ቅድሚያ እንዲሰጡ ለሁሉም አሽከርካሪዎች ጥብቅ መመሪያ መተላለፉንም መግለጫው አመልክቷል።

የዜና ክምችት የዜና ክምችት